አውራውን ፍለጋ… – በተመስገን ደሳለኝ

 
‹‹በድብልቅልቁ አምላክ››
መግቢያ
ዛሬ በስሱ ላነሳው ያሰብኩትን አጀንዳ አለቃ አፅሜ በምኒልክ ዘመን ካሳተሙት አንድያ መጽሐፋቸው ላይ ባገኘሁት ታሪክ ልጀምር፤ እንዲህም ይነበባል፡-

‹‹በሸዋ መርድ አዝማች ኃይሌ፣ በሣህለ ሥላሴ አልጋ ከተቀመጡ በኋላ ከአቶ ሰይፉ ጋር ቂሙ የማይበርድ የቅድስት ኃይማኖት ጦርነት ተጀመረ፡፡

‹‹በዚያን ዘመን፣ በዚያች ወራት የነበረ ሰው እንዴት ያሳዝናል፤ ታላቅ ሽብር ሆነ፣ ልጅ ሲወለድ ስሙ ‹ሽብሩ› ወይም ‹አሳር አየሁ›› ይባል ነበር፤ የሸዋ መንግስት ከሁለት ተከፈለ፤ አቶ ሠይፉ ከኦሮሞ ጋርና ቴዎድሮስን ከጠላ አባ ሰላማን ከነቀፈ ጋር ሆኑ፤ መርድ አዝማች ኃይሌ ቴዎድሮስንና አባ ሰላማን የወደደን ተከተለ፤ እንደዚህ ጦርነት ሽብር፣ ዘረፋ መጋደል ሆነ፤ በየአውራጃው ‹የአጣ ምን አጣ?›፣ ‹የአገኘ ምን አገኘ?› ተባለ፡፡

‹‹ዳኛ ጠፋ ‹በቴዎድሮስ አምላክ፣ በሰላማ አምላክ፣ በኃይሌ አምላክ፣ በሰይፉ አምላክ፣ በበዛብህ አምላክ› ቢሉ የሚሰማ ታጣ፤ አንድ ባላገር ወንበዴዎች ሲደበድቡት ‹በድብልቅልቁ አምላክ› አለ ይባላል፡››

ይህ የእኛም ዘመን በአፄ ቴዎድሮስ አስተዳደር ወቅት እንደተፈጠረ ከሚነገርለት ‹‹ውጥንቅጡ የወጣ›› ወይም ‹‹የተከፋፈለ አመራር›› ጋር የሚመሳሰልበት ገፅታ እጅግ በርካታ በመሆኑ ‹‹ለምን?›› ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል፤ አዎ! ከመቶ ሃምሳ አመት በኋላ ለምን ወደኋላ ተጎተትን? የህዝባችን ንቃተ-ህሊና ለመዘመን ምቹ ስላልሆነ? ወይስ ጉልበተኛ አሳዳሪዎቻችን መብቱን የሚያውቅ፣ ለምን ብሎ የሚጠይቅ ህብረተሰብ ሰጥ ለጥ ብሎ ለረዥም ጊዜ በዝምታ ሊገዛ አይችልም በሚለው መርሆዋቸው በፈተሉት ሴራ?

በታሪካችን የተሳካለት ለህዝብ የሚበጅ ብቁ አስተዳደር አግኝተን ባናውቅም፣ ቢያንስ በዮሐንስ ዘመን፣ በምኒልክ ዘመን፣ በመንግሥቱ ዘመን፣ በመለስ ዘመን እያልን የምናማርረውና የምንኮንነው (የተጠያቂነቱን ኃላፊነት የምናሸክመው) ‹‹አውራ›› አጥተን ግን አናውቅም፤ ዛሬ ይህ የለም፡፡ በዚህ ፅሁፍም ከኢህአዴግ ውስጥ አውራው መውጣት ይኖርበታል ብዬ የማስበው ፓርቲው በመለስ ሞት ማግስት ወዴት እንደሚሄድ መቸገሩ ራሱንም ሆነ ሀገሪቱን ወደገደል ይከታል ከሚል መነሻ ነው፡፡ የፓርቲው የገዥነት ዘመን እንደሚነግረን ጡንቸኛ ሰው የሆነ ጊዜ ይመጣል፤ አሊያም በያዘው ግራ-ገብና የተበጣጠሰ አሠራር ባልታሰበ ወቅት የተለያዩ ክልላዊ የጦር አበጋዞችን ፈጥሮ መዳረሻ ያሌላትን ሀገር ሊፈጥርብን ይችላል፡፡ እንደልማዱ አንድ ጡንቸኛ ከመሀል ሌሎቹን ጨፍልቆ ከወጣ ምንም ያህል ደመ- ቀዝቃዛ አምባገነን ቢሆን እንኳን ከዚህ ወደከፋ አዘቅጥ ከመንደርደር ይታደገናል ብዬ አስባለሁ፡፡ መቼም ማንኛችንም ብንሆን ይሄ ስርዓት ካለአንዳች ኮሽታ እንዲቀየር እንጂ ከራሱ ሞት ጋር ህልውናችንን እንዲያፋጥን አንፈቅድም (በነገራችን ላይ በዚህ ፅሁፍ ‹‹አውራ››፣ ‹‹መሪ›› የሚለውን ቃል ብቻ ለመተካት እንጂ ‹ምን አይነት መሪ?›፣ ‹ዴሞክራት-አምባገነን?›፣ ‹ቅን-ክፉ?› የመሳሰሉትን ትርጓሜዎችን ለመወከል ጥቅም ላይ የዋለ ቃል ተደርጎ እንዳይወሰድ አስቀድሜ እንዲህ አሳስባለሁ)

የመለስ ህልፈት በሀገሪቱ ላይ ካነበረው ድብልቅልቅ ሁኔታ አንፃር ከአራቱ የኢህአዴግ መስራች ድርጅቶች ‹የአጣ ምን አጣ?›፣ ‹የአገኘ ምን አገኘ?› ብለን ብንጠይቅ በትክክል መልስ የሚሰጠን ማነው? ምክንያቱም ከመለስ በኋላ ሲደረጉ የምናስተውላቸው አንዳንድ ድርጊቶች ‹‹ከመለስ ራዕይ›› አንፃር የሚጣረሱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ገሚሱ የ‹‹መለስን ራዕይ አስቀጥላለሁ›› እያለ እንዳልተገበዘ ሁሉ፣ መለስ ያገደውን ሰልፍ ሲፈቅድ ታይቷል፡፡ ከቤተሰብ አባላት በቀር ማንም እንዳይጠይቃቸው መለስ የከለከላቸውን የህሊና እስረኞች በዘመድ ወዳጅ፣ በአጋር ጓደኛ እንዲጠየቁ ፈቅዷል፡፡ በመለስ ዘመን ለይስሙላ እንኳ የተለየ ሃሳብ የማይነሳበት የፓርላማው ዝግ-በር፣ ዛሬ ተከፍቷል ተብሏል፤ ፓርላማውም ጥርስ እንዳወጣ ተነግሯል – ተነካሹ ማን እንደሆነ ባይገልፅልንም፡፡

በስልጣን ለመቆየት ወሳኝ ከሆኑት ውስጥ አንዱ የሆነው የመከላከያ ሚኒስቴርም ይህንን ያህል አመት ‹‹ባጀትህን አላግባብ አጉድለሀል››  የሚል ጠያቂ አልነበረበትም፤ ዛሬ ‹‹እየጠየቅነው ነው›› ተብሏል፤ እውነት ከሆነ መልካም ነው፡፡ እኔ በግሌ ግን የታጠቀው ሠራዊት በተነሳ ቁጥር ብዙ ጊዜ ትዝ የሚለኝ የፓርቲውን ጥቅም ለማስከበር ወታደራዊ ትምህርቱንና የጠመንጃውን ብቃት ህዝብ ላይ እንዲፈትሽ ሲገደድ ነው፡፡

የሆነ ሆኖ ይህ እስካሁን በቅጡ ያላወቅነው አዲሱ ኃይል (አመራር) ለውጥ እያካሄደ ነው በሚል እሳቤ፣ (ምንም እንኳን ሀገር ሊቀይሩ የሚችሉ መሠረታዊ ለውጦች ባይሆኑም) ለለውጡ መግፍኤው ምንድር ነው? ብለን ብንጠይቅ ለጊዜው ከግምት የዘለለ መልስ ማግኘት የምንችል አይመስለኝም፤ ምናልባትም የስርዓቱ የተለመዱ ‹‹ማስቀየሻ›› ዘዴዎች ወይም መጪውን ምርጫ ታሳቢ ያደረገ አደናጋሪ ስልት ሊሆን ይችላል ብንል እንኳ ሰውየው የነበረው ‹‹ራዕይ›› ሳይሆን ‹‹ቅዠት›› ነበረ ወደሚል ድምዳሜ መገፋታችን አይቀሬ ነው፤ ይህም ነው ‹‹በድብልቅልቁ አምላክ›› እንድንል የሚያስገድደን፡፡

መለስ በህይወት ሳለ ‹‹ጉልበተኛ ነኝ›› ብሎ ስለሚያምን ተቃውሞ ሰልፎች እና ህዝባዊ ሰላማዊ ንቅናቄዎች እንዳይደረጉ በራሱ አንደበት እያስፈራራ ይከለክለበት የነበረው ስልት፣ ዛሬ በፖሊስ የማስጠንቀቂያ መግለጫ ተቀይሯል፤ ይህንን የሚያደርጉት እነማን ናቸው?  የእስልምና እምነት ተከታዮች በሰላማዊ መንገድ ከዓመት በላይ ያነሱትና አሁንም ድረስ እያነሱት ያለው ‹‹የሃይማኖት ነፃነት መብታችን ይከበር›› ጥያቄ በየትኛው መዝገበ ቃላት ነው ‹‹የአክራሪ ኃይሎች የሁከት መንገድ›› የሚል ፍቺ የተሰጠው? በአርሲ፣ ኮፈሌ ከተወሰደው የኃይል እርምጃ ጀርባስ የማን አጀንዳ (ፍላጎት) አለ? ደህና! ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ጊዜ ያስፈልጋል ከተባለ ከችግሩ ሁለት ቀን አስቀድሞ የተሰማው የፌደራል ፖሊስ እብሪት አከል ማስፈራሪያ ይከተሉት ከነበረው ሰላማዊ መንገድ እንዲወጡ ገፍቷቸው ከሆነስ ከዚህ ውጪ ምን አማራጭ ነበራቸው? የሚል ክርክር መነሳቱ አይቀርም (በኮፈሌ የተፈጠረውን ችግር የሰማሁት በኢቲቪ ቢሆንም፣ ብዥታ የፈጠረብኝን አንድ ጉዳይ ልጥቀስ፤ ቴሌቪዥን ጣቢያው ተቀማጭነቱ ኮፈሌ የሆነ ዘጋቢ (ሪፖርተር) እንደሌለው አረጋግጫለሁ፤ ይሁንና ‹‹ሁከተኞቹ›› ዱላና ገጀራ መሰል ስለት ይዘው ተቃውሟቸውን በጩኸት እያሰሙ፣ ከፀጥታ አስከባሪ ጋር ፈጠሩ የተባለውን ግጭት፣ ኢቲቪ ቀርፆ፣ በዜና እወጃው ሰዓት ላይ አቅርቦልናል፤ ደግሞም ዜናውን በቦታው ተገኝቶ ያጠናቀረው ተቀማጭነቱ አዲስ አበባ የሆነ፣ ያውም መዝናኛ ፕሮግራም ላይ የሚሰራ ኤሊያስ አማን የተባለ ጋዜጠኛ ሲሆን፣ በድምፅ መርዶውን ያሰማን ደግሞ ጋዜጠኛ ሳሙኤል ከበደ ነው። እንግዲህ ብዥታ የፈጠረብኝ ወይም ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? የሚል ጥያቄ ያጫረብኝ ይሄ በልቦለድ ዓለም እንኳ ለማመን ፍፁም የሚያዳግት ሁኔታ ነው። ኤልያስ በዕለተ ቅዳሜ የኮፈሌ ነዋሪዎች ሁከት እንደሚፈጥሩ በምን አውቆ አስቀድሞ ከአዲስ አበባ ተነስቶ ቦታው ላይ ደርሶ ሁከቱን ሊዘግብ ቻለ? ምናልባት ለአካባቢው ቅርብ የሆኑት የኦሮሚያ ቴሌቪዥን ጣቢያ ባልደረቦች ዜናውን ቢያዘጋጁት፣ ወይም እንደተለመደው ዘገባው የኢዜአ ቢሆን ኖሮ ይህ ጥያቄ ባልተነሳ ነበር፤ ግን…

‹‹ካፕቴኑ›› ማነው?

የአቶ መለስ ዜናዊን ህልፈት ተከትሎ፣ ሀገሪቱ ብቻ ሳትሆን ‹‹አውራው ፓርቲ›› ራሱ ‹‹አውራ›› አልቦ መሆኑን ለመረዳት ብዙ አለመጠበቃችን እውነት ነው። እርሱ ያለፉትን አስራ አንድ ዓመታቶች (ከ1993-2004 ዓ.ም.) ኢህአዴግን በበላይነት ተቆጣጥሮ፤ ከድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ ይልቅ ጠንካራ መዳፍን በመጠቀም ‹‹ብቸኛ ሰው›› (Strong man) የነበረ መሆኑም እውነት ነው፡፡
እንግዲህ እነዚህ ኩነቶች ናቸው ከመለስ ህልፈት አንድ ዓመት በኋላም የድርጅቱን አቅጣጫ በተመለከተ ለትንተና አዳጋች ያደረጉብን፡፡ ዛሬ የሰማነው መላ-ምት ከወር በኋላ ይቀየራል፡፡ የኃይለማርያም ደሳለኝን ስልጣን በድርጅቱ ውስጥ በተፈጠረው የፖለቲካ ልዩነት ገለልተኛ ለሆነ ጠባቂ እንደተሰጠ አድርገን ብንወስደው አሁንም ግንባሩን የሚዘውረው (የሚመራው) ‹‹ካፕቴን›› ማነው? የሚለው ጥያቄ
የግድ መልስ ይሻል፡፡

ለልዩነት መንስኤ፣ ከዚህ ቀደም ተደጋግሞ እንደተገለፀው ኢህአዴግ አራት ብሄር ተኮር ድርጅቶች የመሠረቱት ‹‹ግንባር›› ቢሆንም፣ አባል ድርጅቶቹ በአንድ ሰው ጠንካራ መዳፍ ስር ቆይተው፣ በእንዲህ ያለ ያልታሰበ አጋጣሚ ነፃ ሲወጡ፣ የተለያዩ ፍላጎቶቻቸውም አብረው ከጠርሙዝ የወጣ ‹‹ጂኒ›› መሆናቸው አይቀሬ ስለነበረ ይመስለኛል፡፡ የኃይለማርያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስትርነት እና የደመቀ መኮንን ምክትልነት ይፋ በሆነ ሰሞን ‹‹ህወሓት ተገፋ›› የሚሉ ድምፆችን አስነስቶ ነበር፡፡ ከጥቂት ወራት ቀደም ብሎ ደግሞ የብአዴኑ ብርሃነ ኃይሉ በደፈናው ‹‹የአፈፃፀም ችግር አለብህ›› ተብሎ ከሀላፊነቱ በተነሳ ማግስት ሌላኛው የድርጅት ጓዱ መላኩ ፈንቴ በ‹‹ሙስና››  መከሰሱ (ምናልባት ብርሃነ የፍትህ ሚኒስትር በመሆኑ መላኩን ለማሰር የወጣውን ‹‹የክስ ቻርጅ›› አልቀበል ብሎ ይሆን ‹‹የአፈፃፀም ችግር›› የተባለው?)፤ እንዲሁም ‹‹የመለስ ተተኪ ባለጊዜ›› የሚል ግምት የተሰጠው በረከት ስምኦንም ከነበረበት ስልጣን ተነስቶ (በተለምዶ ‹‹የስራ ፈት ቦታ›› በሚባለው) በ‹‹አማካሪ››ነት መመደቡ ‹‹የተሸነፈው የህወሓት ኃይል አንሰራራ›› ወደሚል ጠርዝገፍቶታል፤ ወይም ከ‹‹ኃይለማርያም ጀርባ›› አለ ተብሎ ይታሰብ የነበረው ኃይል እንደ ተሸነፈ የሚያስቆጥር መስሏል፡፡ በአናቱም በአንዳንድ የሚኒስትርና የዳይሬክተር ቦታዎች ላይ የደኢህዴን አባላት መሾማቸው ኃ/ማርያም ‹‹የደቡብ ሰዎችን ወደፊት አምጥቶ ራሱን/ስልጣኑን ለማጠናከር እየሞከረ ነው›› የሚል ጉርምርምታ እየፈጠረ እንደሆነ እዚህ ጋ መነሳቱ አይከፋም፡፡

እነዚህ ኩነቶች ናቸው ሀገሪቱን (ገዥው ኢህአዴግን) ማን እየመራ (እያሽከረከረ) ነው? የሚል ጥያቄ እንድናነሳ የሚያስገድዱን፤ ሌላው ቀርቶ ህዝብን እያስፈራራ ያለውን ኃይል በቅጡ ማወቅ አልተቻለም፡፡ በቀኝ እጁ የአደባባይ ተቃውሞ ሠልፍ እየፈቀደ፣ በግራ እጁ የሚያግደውስ ማነው? ፍትህ፣ ፍኖተ-ነፃነት እና ልዕልና ጋዜጦችን፣ አዲስ ታይምስ መፅሔትን ማነው በህገወጥ መንገድ ያፈነው?  የእስልምና እምነት ተከታዮች የሃይማኖት ነፃነታቸው እንዲከበር ጥያቄያቸውን ለመንግስት ያቀርቡላቸው ዘንድ የመረጧቸውን የኮሚቴ አባላትስ በ‹‹አሸባሪ››ነት ከስሶ ያሰረው ማነው? …ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀርባ አድፍጧል ይባልለት የነበረው ብአዴንና በስሩ ያደሩ የመሰሉን ኦህዴድና ደኢህዴን? ወይስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያንሰራራ ያለው የህወሓት ኃይል? ወይስ አንደኛውን የህወሓት ክንፍ ይዟል ሲባል የነበረው የእነአባይ ወልዱ ቡድን? ወይስ ራሱ ኃይለማርያም ደሳለኝ ይሆን የ‹‹ወንበሩ››ን ስልጣን ተጠቅሞ ‹‹አሳር አየሁ››ን ታሪክ የደገመው? ጥያቄዎቻችንም እነኚህ ናቸው፤ ወዴት አቤት እንበል? ‹‹ኧረ! በባንዲራው›› ብለንስ ማንን እንማፀን?

የ‹‹ራዕዩ›› ነገር
አቶ መለስ ህይወቱ ካለፈ ድፍን ዓመት ሞልቶታል፤ ለአጠፋውም ሆነ ለአለማው ታሪክ ካልሆነ በቀር፣ ህግም ሆነ ፖለቲካዊ አሠራር ሊጠይቀው አይችልም፡፡ ሆኖም ዛሬ እንዲህ ድብልቅልቁ ከመውጣቱ በፊት ሲነግሩን የነበረው ‹‹ራዕዩ›› ዛሬም ቢኖር በወደድኩ፤ ራዕይ የሌለው ህዝብ የትም አይደርስምና፡፡ ነገር ግን ይህ ባዶ ምኞት ብቻ እንደሆነ አውቃለሁ፤ ጓዶቹም ያውቃሉ፤ ሌላው ቀርቶ መለስ ለእነሱም ሳይቀር አስፈሪ መሪ ብቻ ሳይሆን ‹‹ጠቅላይ›› እንደነበረ ያውቃሉ) የመለስ አገዛዝ አስከፊነቱ ጉልበተኝነቱ ብቻ መች ሆነና፤ ከለታት አንድ ቀን በእንዲህ ያለ መልኩ ማለፌ አይቀርም በሚል ተተኪ ማፍራት አለመቻሉም ጭምር ነው፡፡ ለአንድ ህዝብ የስኬት ጉዞ ‹‹ራዕይ››  ብቻውን የትም አያደርሰውም፡፡ ራዕዩን አሳምኖ እና አስተባብሮ የሚመራው ‹‹አውራ›› የግድ ይፈልጋል፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ሁለቱም የሉም፤ ታዲያ ማነው ‹‹እናስቀጥለዋለን›› ሲባል የነበረውን ‹‹ራዕዩ››ን የሰለበው? ‹‹አውራ››ውንስ የሰወረው ማነው? ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣ ጀምሮ እስኪሰለቸን ከነገረን ‹‹ውጥኖቹ›› ስንቶቹ መከኑ? ስንቶቹስ ፖሊሲዎቹስ ከሸፉ? በፀደቀበት አዳራሽ በስሜት ንጦ በጭፈራ ያዘለለው ‹‹ህገ-መንግስት››ንስ ስለምን ማክበር ተሳነው? ይህ ሁሉ ‹‹ሽብሩ›› እና ‹‹አሳር አየሁ›› መንስኤው ማን ነው?

በየተቋማቱ ኃላፊነቱን ከፖለቲካ አድልዎ በፀዳ መልኩ በታማኝነት እየተወጣ ያለው ማነው? ገንዘብ ሚኒስቴርስ በአስተዳዳሪነት የተረከበውን ገንዘብ እንዲህ በዋል-ፈሰስ ሲባክን ማን ይጠይቀው? የእግር ኳስ አለቆች እንኳን ማንም ተርታ ተመልካች ሳይቀር የማይሳሳተውን ስህተት ሰርተው፣ የሀገርን ጥቅም ጎድተው ሲያበቁ በእገሌ እና እገሌ አሳብበው፣ በስልጣናቸው ሲቀጥሉ ማን ይጠይቃቸው? ህግ አስከባሪ የሚባሉት ዳኞችስ ስርዓቱ ያልወደደውን ‹‹ኧረ በሕግ!›› እያሉ ወህኒ ሲጥሉ ‹‹ሃይ›› የሚላቸው እንዴት ጠፋ?

በሌላኛው ሰፈር፡- ተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅቶች ራሳቸው ላፀደቁት መተዳደሪያ ደንብ የሚገዛ፣ ዲሞክራት አውራ ማብቃት ስለምን ተሳናቸው? በየጊዜው በውሃ ቀጠነ የአመራር አባላቶቻቸውን ማገዳቸውስ እውን ለፓርቲው ጥቅም ሲባል ነው? ለውጥ እናመጣለን ብለው የተቀላቀሏቸውን አባላትስ ግልፅ ያልሆነላቸውን በጠየቁ ዕለት ‹‹ወያኔ›› እያሉ የሚፈርጁበት ማስረጃ ምንድር ነው? ለግል ጥቅምና ለዝና የተቀላቀለውን፣ ከልቡ ለውጥ ከሚፈልገው መለየቱ ይህንን ያህል ከባድ የሆነባቸው ምስጢሩ ምን ይሆን?

ሀገሪቱ በሁሉም ረገድ አውራ አልቦ ሆናለች፤ የምድሪቱ ማህፀን ይህንን ጉድለት መሙላት ያልተቻለው ስለምንድር ነው? ‹‹መሲሁ››ስ መቼ ይሆን የሚመጣው? ወይስ በሰሜን አሊያም በባሌ ተራራ መሽጐ የተፃፈለትን የመከሰቻ ቀን እየጠበቀ ይሆን? አደባባዩስ ስለምን ጭር አለ? ሌላው ቢቀር የጥንቱን የጎበዝ አለቃ ያህል ‹‹አውራ›› እንኳ ስለምን አጣን? ‹‹ደጋፊ አጨብጫቢ›› ሳይሆን ‹‹መካሪ ለሀገር
ተቆርቋሪ›› አዛውንት ስለምን ጠፋ? የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን ጠማማን የማቅናት፣ ትውልድን የማነፅ፣ ጥፋትን የማረም የአስተምህሮ መንገድ የሚከተል አቻስ ከወዴት መሽጓል? እኮ! ስለምን ረቢ አልቦ ሆንን?

በመጨረሻም መውጫ፡-

በኢህአዴግ ውስጥ የተፈጠረውን ልዩነት ማን በበላይነት እየመራ እንደሆነ ማወቅ አለመቻላችንን የምትገልፅ ተመሳሳይ ታሪክ አሁንም ከአለቃ አፅሜ መጽሐፍ ልጥቀስና ልሰናበት፡- ነገሩ በራስ አሊ (ወራ ሸይክ ስርወ-መንግስት) ዘመን የተፈፀመ ነው፤ ‹‹በራስ ዓሊ ዘመን ሰሜንና ትግራይን የሚገዛ ደጃች ውቤ የሚባል በኦሮሞዎች ተቆርቆሮ፣ አቡነ ሰለማን ይዞ፣ ራስ አሊን ሊወጋ ዘመተ፤ ደብረ ታቦር አጠገብ አጅባር ላይ ተዋጉ፣ ራስ ዓሊም እስከ የነጆ፣ እስከ ገራገራ ሸሹ፤ ደጃች ውቤንና አቡኑን ብሩ አሊጋዝ ማረካቸው፤ ድል የራስ ዓሊ ነበረ፤ አንዱ ሰው ላንዱ ወሬን ጠየቀው፤ ያም ‹ራስ ዓሊን ደጃች ውቤ ተዋጉ› ሲል መለሰለት፤ ‹እህስ› አለው ‹ራስ ዓሊ ሸሹ፣ ደጃች ውቤ ተማረኩ፣ ተያዙ› አለው፤ ‹በወግ አታወራም› ቢለው ‹እነሱ በወግ ያልሆኑትን እኔ ምን ብዬ ላውጋው› አለው›› እናስ! ብዙዎቻችን የድህረ-መለስ ኢህአዴግ ሊሄድበት ይችላል እያልን የቢሆን ዕድሎችን (Scenarios) ከመናገር ውጪ ጥብቀት ያለው መደምደሚያ ላይ መወያየት ብንቸገር ምን ይገርማል!?

ኢትዮሚድያ – Ethiomedia

Advertisements
Aside | This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s