የሳምንቱ አጫጭር ዜናዎች

የሳምንቱ አጫጭር ዜናዎች ከተለያዩ ምንጮች

water line

August 19, 2013  10:03 pm  By Leave a Comment
 
ነዋሪዎች በውሃ እጦት ተሰቃየን አሉ

በሳምንት አንድ ቀን ውሃ ማግኘት ብርቅ የሆነባቸው ሰፈሮች፣ በውሃ እጦት አካባቢያቸውን በመጥፎ ጠረን የሚበክሉ የኮንዶሚኒየም መኖሪያዎች፣ ለተደጋጋሚ አቤቱታ ምላሽ ሳያገኙ በርካታ ወራት እየተቆጠሩ የሚማረሩ ነዋሪዎች የአዲስ አበባ የዘመኑ ገጽታ ሆነዋል፡፡

በቂ ውሃ ስለሌለ በራሽን ለማከፋፈል እየሞከረ መሆኑን የሚልፀው የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በበኩሉ፤ የኤሌክትሪክ መቆራረጥና የአንዳንድ ሰራተኞች እንዝህላልነት፣ ለመንገድ ግንባታ የሚቆፈሩ ቧንቧዎች እንዲሁም በከንቱ የሚባክን ውሃ መብዛቱ የውሃ እጥረትን እንዳባባሱ ይናገራል፡፡

የአገሪቱ እንዲሁም የአህጉሪቱ መዲና በሆነችው ከተማ፣ ለዚያውም በሰለጠነ ዘመን በርካታ ነዋሪዎች የዝናብ ውሃን ደቅኖ ለማጠራቀም ሲሯሯጡና በጀሪካን ተሸክመው ውሃ ሲያመላልሱና የፎቅ ደረጃዎችን ለመውጣት ሲውተረተሩ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡

በገርጂ፣ አየር ጤና፣ ጀሞ፣ እንቁላል ፋብሪካ፣ አዲሱ ገበያ፣ እንዲሁም በየአቅጣጫው የተገነቡ ኮንዶሚኒየሞችን ጨምሮ በርካታ የከተማዋ ሰፈሮች፣ በውሃ እጥረት የተቸገሩ ነዋሪዎች “አወይ ስልጣኔ” በማለት መላ እንደጠፋባቸው ይገልፃሉ፡፡

የፉሪ አካባቢ ነዋሪ ወ/ሮ አልማዝ ሞገስ፣ ቀድሞም ቢሆን በሁለት በሶስት ቀን ነበር ውሃ የምናገኘው ይላሉ፡፡ አሁን ግን ብሶበታል፣ ይሄውና በሰፈሩ ውሃ ካገኘን ከሳምንት በላይ ሆኖናል የሚሉት ወ/ሮ አልማዝ፤ ውሃ የምናገኘው ጀሪካን ተሸክመን ሰፈር አቆራርጠን ነው ብለዋል፡፡ ብዙ ጊዜ አቤቱታ አቅርበን ደከመን፤ ምንም መልስ አላገኘንም ብለዋል – ወ/ሮ አልማዝ፡፡

በጀሞ ቁጥር 1 መኖር ከጀመረች ሁለት አመት የሆናት ሰናይት ፈቃደ በበኩሏ፣ የውሃ ችግር የጠናብኝ ዛሬና ትላንት አይደለም፣ በጣም ቆይቷል ትላለች፡፡ ድሮ ድሮ ሌሊት ላይ ብቅ ይል የነበረው ውሃ፤ ዛሬ ሽታውም የለም የምትለው ሰናይት፣ የኮንዶሚኒየም ቤት ያለ ውሃ የስቃይ ቤት ማለት ነው ብላለች፡፡ የመጀመሪያ ፎቅ ነዋሪዎች የዝናብ ውሃ ደቅነው ለማጠራቀም ይሞክራሉ፣ ሁለተኛና ሦስተኛ ፎቅ ግን አይሞከርም፡፡ ቧንቧ በየቤታችን አለ፤ ውሃ የምናመጣው ግን እንደ ጥንቱ የገጠር አኗኗር ነው የምትለው ሰናይት፤ ለውሃና ፍሳሽ አመልክተናል፡፡ ውሃውን ወደ ላይ ለመሳብ የፓምፕ ሃይል ስለሚያስፈልግ ነው ይሉናል፤ ይህንን እንደ በቂ ምላሽ ይቆጥሩታል በማለት ግራ መጋባቷን ትገልፃለች፡፡

ጀሞ ብቻ አይደለም፡፡ የጐሮ ነዋሪ ናርዶስ አስማረ አንድ ቀን ውሃ ከመጣ ለሁለትና ለሶስት ቀን ይጠፋል፤ ቅዳሜና እሁድ ውሃ ያገኘንበት ጊዜ የለም ትላለች፡፡ በየሳምንቱ አቤቱታ ስናቀርብ የምናገኘው ምላሽ ሁልጊዜ ተመሳሳይ ነው የምትለው ናርዶስ፤ አሁን ይስተካከላል ይሉናል፤ ግን ተስተካክሎ አያውቅም ትላለች፡፡

ውሃ የሚጠፋበትን ቀን ዘርዝሮ ከመናገር ይልቅ ውሃ የሚመጣበትን ቀን መናገር ይቀላል የሚለው የአዲሱ ገበያ ነዋሪ ልዩነህ አያሌው፤ ውሃ ይግባልን ብንል ይሻላል፤ በሳምንት አንዴ ውሃ ከመጣ ፌሽታ ነው፤ ብርቅ ይሆንብናል ሲል ይናገራል፡፡

አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ ወ/ሮ እፀገነት ተስፋ ምላሽ ሲሰጡ፤ በአዲስ አበባ የውሃ ችግር አለ በማለት ነው የሚጀምሩት፡፡ ዋናው ምክንያት የውሃ እጥረት ነው የሚሉት ወ/ሮ እፀገነት፤ ከነእጥረቱም ቢሆን ውሃውን ለህብረተሰቡ ለማድረስ ደግሞ የተለያዩ መሰናክሎች እንደሚገጥሙ ገልፀዋል፡፡ ኤሌክትሪክ ሲቋረጥ ከፍታ ቦታ ላይ ለሚገኙ ነዋሪዎች በፓምፕ ውሃ ማድረስ አንችልም ይላሉ፡፡

ሌላው ችግር በራሳችን ሰራተኞች የሚፈጠር ነው የሚሉት ሃላፊዋ፣ የውሃ ቧንቧ ተበላሽቷል ተብሎ ሲነገራቸው አንዳንድ ሰራተኞች ብልሽቱን እንደመጠገን ውሃውን ዘግተውት ይመጣሉ ብለዋል፡፡ በመንገድ ስራና የተለያዩ ግንባታዎች የውሃ ቧንቧ እንደሚሰበር ሲያስረዱ፣ ለምሳሌ በሃያ ሁለት አካባቢ፣ በመንገድ ግንባታ ምክንያት ዋናው የውሃ ቧንቧ በመቋረጡ አሁን በተዘረጋ ጊዜያዊ ቧንቧ የምናቀርበው ውሃ በአስር እጥፍ ያነሰ ነው ብለዋል፡፡ በዚያ ላይ ለከተማዋ ከሚቀርበው ጠቅላላ የውሃ መጠን ውስጥ ከአንድ ሦስተኛ የሚበልጠው በከንቱ ይባክናል ብለዋል ሃላፊዋ፡፡ (ምንጭ፤ አዲስ አድማስ)

Advertisements
Aside | This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s