ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል ከኖርዌይ ኤምባሲ ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል ዋና ዜና
25 August 2013 ተጻፈ በ 

ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል ከኖርዌይ ኤምባሲ ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል

‹‹ኤምባሲው የገባውን ውልና የኢትዮጵያ ሕግ ጥሶ ቤቴን ተቆጣጥሯል›› ኢንጂነር ኃይሉ

‹‹ከኢንጂነር ኃይሉ በተከራየሁት ቤት እ.ኤ.አ. እስከ 2019 የመቆየት መብት አለኝ›› የኖርዌይ ኤምባሲ

ታዋቂው ፖለቲከኛ ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል ለኖርዌይ ኤምባሲ ባከራዩት ቤት ምክንያት ከኤምባሲው ጋር የከረረ ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል፡፡

‹‹ኤምባሲው እ.ኤ.አ. በ2004 በገባው ውል መሠረት ቤቱን ለ15 ዓመታት የመጠቀም መብት ቢኖረውም፣ በውሉ መሠረት ከዚህ ቀደም ኮንትራቱን አፍርሷል፡፡ ነገር ግን ቤቱን ከሕግ ውጭ ተቆጣጥሮ አልወጣም ብሏል፤›› የሚል ቅሬታቸውን እያሰሙ ይገኛሉ፡፡ የኖርዌይ ኤምባሲ በበኩሉ፣ ‹‹ከኢንጂነር ኃይሉ ጋር በ2004 በገባሁት ውል መሠረት ለ15 ዓመት የመጠቀም መብት አለኝ፤›› በማለት ይከራከራል፡፡ 

ጉዳዩን በተመለከተ ኢንጂነር ኃይሉ ሻውልን በመወከል ልጃቸው ዶ/ር ሻውል ኃይሉ ለሪፖርተር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ኤምባሲው የአገሪቱን ሕግ ጥሶ ንብረት መያዙን ይገልጻሉ፡፡ ከኤምባሲው ጋር ላለፉት አሥር ዓመታት መልካም ግንኙነት እንደነበራቸው የሚናገሩት ዶ/ር ሻውል፣ በአባታቸው በኢንጂነር ኃይሉና በኖርዌይ ኤምባሲ መካከል እ.ኤ.አ. በ2004 በተገባ ውል መሠረት የኢንጂነር ኃይሉ ቤት ለ15 ዓመታት ለኤምባሲው መከራየቱን ይገልጻሉ፡፡ ይሁን እንጂ ኤምባሲው በውል ስምምነቱ ላይ ባለው ውል የማቋረጥ መብት አንቀጽ መሠረት እ.ኤ.አ. በጁን ወር 2010 ቤቱን ለመልቀቅ እንደፈለገ በደብዳቤ መግለጹን አስረድተዋል፡፡ 

በተባለው ወቅት ቤቱን ለመልቀቅ አምባሲው ገልጾ የነበረ ቢሆንም፣ ሌላ ተስማሚ ቤት ማግኘት አልቻልኩም በማለት ለአንድ ዓመት ቤቱን እንደማይለቅ ማሳወቁንም አክለው ገልጸዋል፡፡ ኤምባሲው ተስማሚ ቦታና ቤት ማግኘት ባለመቻሉ ሁኔታውን ከግምት በማስገባት ኤምባሲው በመኖሪያ ቤቱን ላልተወሰነ ጊዜ እንዲጠቀም ኢንጂነር ኃይሉ መፍቀዳቸውንና በዚህ መሠረት እንደቆየ ያስረዳሉ፡፡

ነገር ግን ኢንጂነር ኃይሉ ቤቱን በመፈለጋቸው እ.ኤ.አ. በፌብሯሪ 2013 ለኤምባሲው በጻፉት ደብዳቤ፣ ቤቱን እ.ኤ.አ. እስከ ጁን 30 ቀን 2013 እንዲያስረክባቸው እንደጠየቁ ልጃቸው ዶ/ር ሻውል ያብራራሉ፡፡ ኤምባሲው ግን ቤቱን እንዲለቅ ለተጻፈለት ደብዳቤ ፈቃደኛ ባለመሆኑ፣ በተደጋጋሚ ጊዜ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ቢጻፍለትም በእንቢተኝነቱ መጽናቱን ገልጸዋል፡፡ ኢንጂነር ኃይሉ ቤቱን ለመሸጥ መፈለጋቸው የተነገረው የኖርዌይ ኤምባሲ ራሱ ለመግዛት ፍላጐት ማሳየቱን፣ ነገር ግን ዋጋው ተወደደ በሚል ምክንያት የመግዛት ፍላጐቱን ሰርዟል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በተቀበለችው የቪዬና ኮንቬንሽን መሠረት ኤምባሲው ያለመከሰስ መብት ያለው በመሆኑ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መውሰድ አለመቻሉን ዶ/ር ሻውል ገልጸዋል፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጣልቃ እንዲገባ ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡ ‹‹የሚኒስቴሩ የሕግ ዳይሬክቶሬት ኤምባሲውንና እኛን ለማግባባት ያደረገው ጥረትም ውጤት አላመጣም፤›› ሲሉ ዶ/ር ሻውል ያስረዳሉ፡፡ ‹‹አንድ ኤምባሲ በመጀመሪያ ሊያከብር የሚገባው የሚገኝበትን አገር ሕግ ነው፤›› የሚሉት ዶ/ር ሻውል፣ የኖርዌይ ኤምባሲ ግን የኢትዮጵያን ሕግ በመጣስ የኢንጂነር ኃይሉን የንብረት ባለቤትነት እየተጋፋ ይገኛል ብለዋል፡፡ 

በሁለቱ መካከል ስለተነሳው ውዝግብ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሕግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ረታ ዓለሙ ማብራሪያ እንዲሰጡ ቢጠየቁም፣ ‹‹ምንም የምሰጠው አስተያየት የለም፤›› ብለዋል፡፡ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተፈጠረውን ችግር በማግባባት ለመፍታት ያደረገው ጥረት ውጤት የሌለው በመሆኑ ፍርድ ቤት እንዲዳኛቸው የኤምባሲውን ፈቃደኝነት ቢጠይቁም፣ ኤምባሲው እንቢተኛ መሆኑን ዶ/ር ሻውል ያስረዳሉ፡፡

የኖርዌይ ኤምባሲ ምክትል ጉዳይ አስፈጻሚ የሆኑት ቶቭ ስቱብ በተፈጠረው አለመግባባት ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹እ.ኤ.አ. ከኢንጂነር ኃይሉ ጋር የገባነው ውል ቤቱን በኤምባሲነት ለ15 ዓመት እንድንጠቀም ይፈቅድልናል፤›› ብለዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ የኖርዌይ የቀድሞ አምባሳደር እ.ኤ.አ. በማርች 2009 ለኢንጂነር ኃይሉ የጻፉት ደብዳቤ የሁለቱ ወገኖች ዋነኛ መከራከሪያ ነው፡፡

ሪፖርተር አምባሳደሩ ጻፉ የተባለውን ደብዳቤ የተመለከተ ሲሆን፣ የደብዳቤው ይዘት ኤምባሲው ቤቱን እ.ኤ.አ. በጁን ወር 2010 የመልቀቅ ዕቅድ እንዳለው የሚያስረዳ ነው፡፡ በውል ስምምነታቸው መሠረት ኤምባሲው ስምምነቱን ለማፍረስ የሦስት ወራት ማስጠንቀቂያ መስጠት ያለበት መሆኑን ያስረዳል፡፡ በመሆኑም ኢንጂነር ኃይሉ ኤምባሲው በማርች 2009 የጻፈው ደብዳቤ ዋናውን የኪራይ ውል ያፈርሰዋል የሚለው ዋነኛ መከራከሪያቸው ነው፡፡ ኤምባሲው በበኩሉ ይህ ደብዳቤ የኤምባሲውን የወደፊት ዕቅድ የሚያስረዳ እንጂ፣ ውሉን ለማፍረስ በማስጠንቀቂያነት የተጻፈ አይደለም በማለት መከራከሪያ ያቀርባል፡፡ 

ሁለቱ ወገኖች በመካከላቸው የተፈጠረውን አለመግባባት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል መቅረፍ አለመቻላቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡ በተጨማሪም ኤምባሲው ያለመከሰስ መብት ያለው በመሆኑ ኢንጂነር ኃይሉ ወደ ፍርድ ቤት መሄድ አለመቻላቸው ታውቋል፡፡ የተነሳው ውዝግብ እንዴት ሊቋጭ ይችላል በሚል ዶ/ር ሻውል ላቀረብንላቸው ጥያቄ፣ ‹‹መብታችንን ለማስከበር የራሳችንን ዕርምጃ እንወስዳለን፤›› ብለዋል፡፡ ለዚህ የሚሰጡት ምክንያት ኤምባሲው ውሉን በማፍረሱ በአሁኑ ወቅት ቤቱ እንደተሸጠና በሽያጭ ውሉ መሠረት ደግሞ ቤቱን ለገዛው አካል እ.ኤ.አ. ጁን 30 ቀን 2013 ማስረከብ የነበረባቸው መሆኑን ነው፡፡ 

‹‹በሽያጭ ውሉ መሠረት ቤቱን ማስረከብ ባለመቻላቸው ለእያንዳንዱ ቀናት ሁለት ሺሕ ዶላር በቅጣት ለመክፈል፣ እንዲሁም ውሉን የሚያፈርስ ወገን አንድ ሚሊዮን ብር ለመክፈል ስምምነት አድርገናል፤›› በማለት የሚያስረዱት ዶ/ር ሻውል፣ ኤምባሲው ቤቱን ባለመልቀቁ ምክንያት የሚጣልብንን ሁለት ሺሕ ዶላር ቅጣት አደጋ ውስጥ የሚከት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

‹‹ከዚህ በተጨማሪ አባቴ ኢንጂነር ኃይሉ በጠና የጤና ችግር ውስጥ በመሆኑ ሕክምና ያስፈልገዋል፡፡ መብታችንን አስከብረን አባቴንና ቤተሰቤን መታደግ ይገባኛል፤›› ብለዋል፡፡ ለዚህም አስፈላጊ ያሉትን ዕርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደዱ ገልጸዋል፡፡ አስፈላጊው ዕርምጃ ለጊዜው ምን እንደሆነ መግለጽ አልፈለጉም

Advertisements
Aside | This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s