Friday, August 30, 2013

ድምፃችን ይሰማ ኢሕአዴግ በጠራው ሰልፍ ላይ በመገኘት አክራሪነትን እንደማይደግፍ በመግለጽ ኢሕአዴግን ሊያሳፍረው ነው

 

ከድምጻችን ይሰማ

የትኛውንም አይነት አክራሪነት ሙስሊሙ ህብረተሰብ እንደሚያወግዝ በእሁዱ ሰልፍ በአደባባይ ያስመሰክራል!

ጁምአ ነሐሴ 24/2005
‹‹አክራሪነትን ሕገ-መንግስቱ ቢፈቅድ እንኳን አንቀበለውም!›› ኮሚቴዎቻችን
ለዚህች አገር ሰላም እና ደህንነት መንግስትን ጨምሮ ሁሉም ወገን ከአክራሪነት ሊርቅ ይገባዋል!

አክራሪነት ማለት ድንበር ማለፍ ማለት ነው፡፡ አክራሪነት ዜግነት የለውም፣ በእምነት አይወሰንም፣ በቦታ አይከለልም፣ በሐገር አይለይም፡፡ በግል፣ በህብረት፣ በመንግስት ደረጃ ሊከሰት የሚችል ነው፡፡ አክራሪነትን ከማንም በፊት ያወገዙት ነብያችን (ሰ.ዐ.ወ) ስለሆኑና የጥፋት አቅጣጫ መሆኑን ስለጠቆሙን አክራሪነትን ለመቃወም ከማንም በፊት ቀድመን የምንገኘው እኛው ነን፡፡ አክራሪነትን የምንቃወመው መሰረታችን ለአክራሪነት የሚመች ስላልሆነ ነው፡፡ ተቻችሎ መኖርም ቋሚ አጀንዳችን ስለሆነ ነው፡፡ ለዚህች አገር በሰላም መኖር ሁሉም ወገን ከሁሉም አይነት አክራሪነት ርቆና እውነተኛ የሰላም ፈላጊ ሆኖ መኖር አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ ህዝቦች በጋራ በተግባቡበት ህግ በሰላም የመኖር፣ በሃይማኖቶች መካከል መከባበር የአስተምህሮታችን መሰረት ሲሆን በሚሊዮኖች ፊርማ ወክለን በግፍ የታሰሩትን ኮሚቴዎቻችንን ጨምሮ መስዋእትነት የምንከፍልለት ሰላማዊ ትግላችን በኢትዮጵያ የሃይማኖት ነፃነት እና የሃይማኖቶች ተከባብሮ የመኖር ሂደት አካል ነው፡፡ አክራሪነት ማለት ግን ዛሬ ፖለቲከኞች እንደሚጠቀሙት ተለክቶ እንደሚሰፋ ልብስ ሊያጠቁት የሚፈልጉትን አካል ሁሉ በልክ በልኩ አሰፍተው አልብሰው የሚያጠቁበት መቆመሪያ አይደለም፡፡

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ለሁለት አመታት ስንቃወም የኖርነውም መንግስታዊ ሃይማኖት (አህባሽ) በመንግስት ሙሉ እቅድ እና ትግበራ አማኞችን ለመከፋፈልና የእርስበርስ ፀብ ለመፍጠር ከሌሎች ሃይማኖቶችም ጋር አብሮ የመኖር ገመድን ሊበጥስ ‹‹ከመንግስት የወረደ ነውና ተቀበሉት›› ተብሎ ስለተጫነብን ነው፡፡ መሪዎቻችንም ሆኑ በሺ የሚቆጠሩ ንፁሃን በእስር የሚማምቅቁት ብሎም በርካቶች የሞቱትና የተደበደቡት ‹‹እኔ ከመረጥኩላችሁ ውጭ ትክክለኛ እምነት የለም›› የሚልን አክራሪነት በመቃወም እንጂ በሌላ አይደለም፡፡ መንግስት የእምነት መብት መጠየቃችንን አክራሪት ሲል ፈርጆታል፡፡ ይህ መብት መጠየቅን በአክራሪነት የሚፈርጅ ፖለቲካዊ አክራሪነትን በፅኑ እናወግዛለን፡፡ በሃገራችን ተጨባጭ ፅንፈኛ የፖለቲካ አካሄድ የትክክለኛው አክራሪነት መፈልፈያ መሆኑን እያየን ነው፡፡ በዚህ አክራሪነት ከማንም በላይ የተጠቃነው እኛ ነንና አክራሪነትን በፅኑ እናወግዘዋለን፡፡ ይህንንም ለማሳየት ነው የእሁዱን ሰልፍ የምንሳተፈው፡፡
የነሃሴ 26 ሰልፍ ህዝበ ሙስሊሙ ከሌላ ሃይማኖት ተከታይ ወንድሞቹ ጋር የሚገናኝበት፣ ስለሃገሩ ስላም ያለውን ቀናዒነት የሚያሳይበት መድረክ በመሆኑ ሙስሊሙ ከሌሎች ሃይማኖት ተከታይ ወንድሞቹ ጋር ሰላምታ በመለዋወጥ አድራሻ በመለዋወጥ ጠንካራ አብሮነትን የሚያጠናክርበት ነው፡፡ ትናንት የጥምቀት በዓሉን ታሳቢ በማድረግ የተቃውሞ መርሃግብሩን የከለሰለትና ቦታ ከቀየረለት ህዝበ ክርስቲያን ጋር ነሃሴ 26 በአንድነት ቆሞ አክራሪነትን በጋራ እያወገዘ ሰላማዊነቱን ያስመሰክራል፡፡ በተጨማሪም የነሃሴ 26 የቅዋሜ መድረክ ከሁሉም እምነት ተከታዮች ጋር ያለንን ትስስር የምናጠናክርበትና ሰላማዊ የመብት ጥያቄአችንን ይበልጥ የምናስረዳበት መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ ሰልፉን እንደጠራው የሚነገርለት የሃይማኖት ጉባኤ ውስጥ ያሉ የሃይማኖት አባቶች ለዚህች ሃገር እውነተኛ የሰላም አስተማሪና ተጠሪ መሆናቸውን፣ ለችግሮች መፍትሄ በማፈላለግ በመሰለፍ ሃገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አደራ የምንልበትም ዕለት ነው፡፡
ሰልፉ የሃይማኖቶች ጉባኤ ከሚባለው ተቋም ጋር ህዝብ የሚኖረው የመጀመሪያ የአደባባይ ግንኙነት በመሆኑ የተቋሙን አሰላለፍ በተግባር ለማየት ምቹ አጋጣሚ ነው፡፡ በመሰረቱ የሃይማኖቶች ጉባኤ መንፈሳዊ መሪዎች ያሉበት በመሆኑ ‹‹አክራሪነትን እናወግዛለን›› በሚል መሪ ቃል በጠሩት ሰልፍ የአደባባይ ውንብድና ቢፈፀም በወከላቸው አማኝ እና በተወከሉለት እምነት ላይ ታላቅ ክህደትን መፈፀም ነው የሚሆነው፡፡ መንግስትም ይህንን ሰልፍ ለርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማዋል ከተሯሯጠ በሃገሪቱ እምነት የሚጣልበት ነፃ ተቋም ፈፅሞ አለመኖሩን ማስመስከር ሲሆን በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን ደግሞ ያለ እፍረት መደበኛ ተግባሩ እንዳደረገው ለመላው ኢትዮጵያዊ በገሃድ የሚያውጅበት አጋጣሚ ይሆናል፡፡ በዚህ አጋጣሚም መንግስት ሰልፉን ለሃገራዊ መግባባት እንዲያውለው አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡ ዜጎች በሃይማኖታቸው ተከብረው መብት በመጠየቃቸው ሳይሸማቀቁና ሳይበደሉ የሚኖሩባትን ኢትዮጵያ ለቀጣዩ ትውልድ ለማቆየት መልካም አጋጣሚ በመሆኑ መንግስት እድሉን በአወንታዊ መልኩ ሊጠቀምበት ይገባል እንላለን፡፡
ከዚህ ውጭ ግን ‹‹የሃይማኖቶች ጉባኤ ጠርቶታል›› ለተባለው ሰልፍ ተሳትፎ መንግስት የህዝብን ጓዳ ማስጨነቁ፣ ሰልፉን በማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ በማስፈፀም በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ ገብነቱን በግልፅ እያሳየ ነው፡፡ መንግስት ‹‹አክራሪነትን እዋጋለሁ›› በሚል ሽፋን እምነታችንን ክፉኛ ጣልቃ ገብቶበታል፡፡ አሁን ደግሞ ‹‹አክራሪነትን እናወግዛለን›› በሚል ሽፋን ህዝብን በግዳጅ ጭምር በማስወጣት ይህን ሰልፍ ከሃገራዊ መግባባት ይልቅ ለእኩይ አላማ ሊጠቀምበት አስቦ ከሆነ ተግባሩን በፅኑ እናወግዛለን፡፡ ይህ ተግባር የመንግስት መዋቅር ከዚህ ቀደም ፖለቲካን ሽፋን አድርገው የሃይማኖት እና የቡድን አጀንዳን ለማስፈፀም ለሚሯሯጡ አመራሮች እንደተጋለጠ ሁሉ፤ አሁን ደግሞ በሙሉ መዋቅሩ በሃይማኖት ሽፋን ፖለቲካዊ ቁማር ለመጫወት አስቦ ከሆነ በፅኑ እናወግዘዋለን፡፡
በመሆኑም ይሄን ሽፋን ገልጠን በማውጣትና መንግስት ሊደበቅበት ያሰበበትን ካባ በማውለቅ ‹‹አክራሪነትን አዎ እናወግዛለን!››፣ ‹‹በአክራሪነት ሽፋን ግን በእምነታችን ጣልቃ መግባትንም በተመሳሳይ እናወግዛለን›› ልንል ወደ ሰልፉ እንተማለን፡፡ በሰልፉ ላይ በመገኘት መንግስት ሰልፉን ከተቀመጠለት ስያሜ ውጪ ለህገ ወጥ ተግባሩና ፖለቲካዊ ትርፍ ማጋበዣው መጠቀሚያ እንዳያደርገው እናደርጋለን፡፡ ሃላፊነት በጎደለውና ከልክ ባለፈ ንቀት የሙስሊሙን እምነት ለመበረዝ ሲሞክርና አማኙን በማንገላታት ለመፍጠር የታለመው ሀገራዊ ትርምስ አልሳካ ሲል ዛሬ አሰላለፍን በመቀየር በሃይማኖቶች ሽፋን ህዝብን በህዝብ ላይ ለማነሳሳት የተቀመረ ስሌት ካለ እንደማይሳካ የፊታችን እሁድ በተግባር እናስመሰክራለን፡፡ ይህን ክፉ ራዕይ ዳግም መና ለማስቀረት ዛሬም ከሃገር ወንድምና እህቶቻችን ጋር እምነትና አስተሳሰብ ሳይለየን እጅ ለእጅ በመያያዝ ለዘመናት በገዢዎች ያልተናደውን አንድነታችንን እናጠናክራለን፡፡
የነሃሴ 26 ሰልፍን ስንሳተፍ አክራሪነትን በመቃወም እና አብሮነትና ተቻችሎ መኖርን በተግባር እናሰይበታለን፡፡ ሆኖም አክራሪነትን ከመቃወም ውጭ በሰልፉ ላይ የሚስተናገዱ ማንኛውንም አይነት አፍራሽ መርሃ ግብሮች ካሉ በፅኑ እናወግዛለን፡፡ ሁሌም ደጋግመን ስንገልጸው እንደነበረው ሁሉ የሙስሊሙ ህብረተሰብ ጥያቄም ሆነ እንቅስቃሴ ሰላማዊ፣ አገራዊ እና ህዝባዊ መሆኑን እንዲሁም ይምነት እንጂ የፖለቲካ ጉዳይ አለመሆኑን እና ከመብት እና የፍትህ ጥያቄ ውጭ የተለየ መልክ እና ይዘት እንደሌለው ለሁሉም ኢትዮጵያውያን አሁንም ደግመን ማስረገጥ እንሻለን:: በመሆኑም ሙስሊሙ ኅብረተሰብ በሙሉ ከእነ ቤተሰቡ ነቅሎ በመውጣት በእሁዱ የተቃውሞ መርሐ ግብር ላይ እንዲሳተፍ ጥሪ ተላልፏል፡፡ ሁላችንም እዛው እንገናኛለን፡፡ ለእለቱ ከሚቀመጠው መርሐግብር ክንውን ሳንላቀቀ የተቀመጠውን ብቻ በመፈጸም አክራሪነትን ከሌሎች ኢትዮጵያውን እህቶችና ወንድሞች ጋር በመሆን በተግባር እናወግዛለን፡፡
የነሀሴ 26 መርሐግብር አፈጻጸም በተመለከተ
ጁምአ ነሐሴ 24/2005

በዕለቱ መደበኛውን የሰልፍ መርሃግብር ሙሉ በሙሉ በቋሚነት የምንከተል ሲሆን በተጨማሪ ግን
* ሁሉም የሃይማኖት አባቶች ሰላምን፣ ፍቅርን እና መቻቻልን እንደሚሰብኩ፣ እኩይ ተግባራትን እና አክራሪነትን እንደሚቃወሙና የሰላም እንደራሴዎች እንደሆኑ ለማሳየት እንዲሁም የሃይማኖት አባቶቹ ለወከሉት እምነትና በእምነቱ ስር ላሉ አማኞች ያለንን ክብር ለማሳየት ንግግር በሚያደርጉበት ወቅት የማናምንበትን ወይም ሞራላችንን የሚነካ ንግግር ቢያደርጉ እንኳ በጥሞና ንግግራቸውን እናደምጣለን፡፡ በምንም መልኩ የሃይማኖት አባቶቹ ንግግር ሲያደርጉ ንግግራቸው እንዲቋረጥ አናደርግም፡፡ ንግግራቸውን እንዳጠናቀቁም የሰላም መገለጫ የሆነ ነጭ ነገር እናውለበልባለን፡፡ ለዚህም መሃረብ፣ ነጭ ወረቀት፣ ሶፍት እና መሰል ቀላል ነገሮችን መጠቀም እንችላለን፡፡
* ህዝብ በይፋ ባወረደው ህገ-ወጥ የቀበሌ ሹመት የመጡ የመጅሊስ ሹመኞች ንግግር በሚያደርጉበት ወቅት ንግግራቸውን እስኪጨርሱ ያለምንም ድምፅ ሁለቱንም ጆሯችንን በመዳፋችን ደፍነን እንቆያለን፡፡
* ንግግር የሚያደርጉ የመንግስት ባለስልጣናት ካሉ በሚሊዮኖች ፊርማ የወከልናቸው ኮሚቴዎቻችንን በማሰር መላውን መብት ጠያቂ ህዝበ ሙስሊም ያሰሩ መሆናቸውን ለመግለጽና የነጠቁንን መብታችንን በመመለስ ሕዝቡን ከእስራት እንዲፈቱት ለመጠየቅ ንግግራቸውን እስኪጨርሱ ያለምንም ድምፅ ሁለት እጃችንን ወደላይ ከፍ አድርጎ በማንሳትና በማጠላለፍ ምልክት ብቻ እናሳያለን፡፡
ማስታወሻ፡-
– ወደሰልፉ የምንሄደውም ሆነ የምንመለሰው ሌሎች የሰልፉ ተሳታፊዎች በሚሄዱበት ሁኔታ ሲሆን በዋናው መርሐግብር ላይም ሆነ ከዚያ በፊት እና በኋላ ከተጠቀሱት ውጭ ሌላ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ማድረግ በጭራሽ የለብንም፡፡
Short URL: http://www.zehabesha.com/amharic/?
Advertisements
Aside | This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s