የጠ/ሚ ባለቤት በቤተመንግስት ኑሮ መሰላቸታቸውን ገለጹ

 ኢሳት ዜና :-ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ የቤተመንግስት ኑሮ የሚመች አለመሆኑንና የቀድሞ ጠ/ሚኒስትርንም አኗኗር በማየት ያዝኑ እንደነበር ተናግረዋል።

ቀዳማዊት እመቤቷ ትላንት ከወጣው መንግስታዊው ዘመን መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የቤተመንግስት ሕይወት አስደሳች አይደለም ብለዋል፡፡ “ የቤተመንግስትን ሕይወት ለማንም ተመኝቼው አላውቅም፡፡ የሴቶች ጉዳይን ስናቋቁም ስምንት ወር ተመላልሼበታለሁ፡፡ ዛሬ እናንተ ተፈትሻችሁ እንደገባችሁት እኛም ተፈትሸን ነበር የምንገባው፡፡ እዚህ ግቢ ስገባ ወደጠ/ሚኒስትሩ ቤተሰቦች መኖሪያ ማዶ እያየሁ አዝንላቸው ነበር፤ግን ለሰው አላወራም፡፡ እዚህ ግቢ ውስጥ የሚኖር ሰው እንዴት ተበድሎአል እያልኩ እገረም ነበር፡፡ እና እኔን ኑሪ ቢሉኝ የማላደርገው መስሎ ይሰማኝ ነበር፡፡    ብለዋል፡፡

አስተዳደጌ ያስተማረኝ ከሌሎች ጋር በጋራ መኖርን ነው ያሉት ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ራስን ለማዝናናት፣ዞር ብሎ ቡና ለመጠጣት ፣ዘመድ ጓደኛ እንደልብ ለማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን በመጥቀስ ከዚህ አንጻር  የቤተመንግስት ሕይወት ነጻነት የለውም ሲሉ አስረድተዋል፡፡

“ለአንዳንዶች የቤተመንግስት ሕይወት የተንደላቀቀ መስሎ ይሰማቸዋል” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም በአጭሩ እንደሚታሰበው ዓይነት አይደለም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የቀድሞ ኑሮአቸው ከአሁኑ በምን ይለይ እንደሆነ ተጠይቀውም የምግብ ማብሰያውና የአዘገጃጀቱ ሁኔታ ለየት እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡ “ቤተመንግስት የበሰለው ነገር በንጽሕና የሚቀርብበት ነው፡፡ አዘጋጆቹ በዘርፉ ሙያው ያላቸው ናቸው፡፡ ብዙ ዓመት ያገለገሉ ወጥ ቤቶች አሉ፡፡ ከዚህ ውጪ እንግዲህ ጥበቃው አለ፤ይህው ነው” በማለት አስረድተዋል፡፡

ወ/ሮ ሮማን ከጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አብራክ የወለዱዋቸው የ23፣የ20 እና የ18 ዓመት ሶስት ሴት ልጆች እንዳሉዋቸውም በቃለምልልሳቸው ተናግረዋል፡፡

ባለቤታቸው አቶ ኃይለማርያም በአመራራቸው አስቸጋሪ ሁኔታ ያጋጥማቸው እንደሆን ተጠይቀውም ሲመልሱ አስቸጋሪ ነገር እንኩዋንስ አገር የሚያክል ነገር በመምራት ላይ ቀርቶ ታችም ሞልቱዋል፡፡ “አሁን ያለንበት የግሎባላይዜሽን ዘመን ነው፡፡ ብዙ ዓለምአቀፋዊ ይዘት ያላቸው ጠቃሚም ጎጂም ነገሮች አሉ፡፡ የኢትዮጽያ ሕዝብ አሁን ለመብቱ መታገል ተለማምዶአል፤ መጠየቅን ለምዶአል፡፡  ፈጣን ዕድገትን ይፈልጋል፡፡ ሠላምን፣ ተረጋግቶ መኖርን ይፈልጋል፡፡ መልካም አስተዳደርን ይፈልጋል፤ መልካም አስተዳዳር ሲባል ደግሞ በውስጡ ብዙ ጉዳዮች አሉት፡፡ እና ይህን ሁሉ ፍላጎት ይዞ ሕዝብን የሚያረካ አመራር መስጠት እያደገ የሚሄድ ነው” ብለዋል፡፡

ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ከቀድሞዋ እመቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ቤተመንግስቱን ተረክበው ከባለቤታቸውና ልጆቻቸው ጋር የቤተመንግስት ኑሮ ከጀመሩ ገና አንድ ዓመት አልደፈኑም፡፡

ወ/ሮ ሮማን የቤተ-መንግስት ኑሮ ነጻነት እንዳይኖረው የተደረገበትን ምክንያት አላብራሩም፣ ነጻነት እንዲኖረው ለማድረግም ምን ምን እርምጃዎች መወሰድ እንዳለባቸው አልዘረዘሩም። ወ/ሮ ሮማን  ህዝቡ ስለመብቱ መታገል ተለማምዷል በማለት መናገራቸው በቅርቡ የተቃዋሚ ድርጅቶች ካደረጉት ሰልፍ ጋር ይያያዝ አይያያዝ ወይም፣ ይህ ልምምድ ከአቶ መለስ ዜናዊ ሞት በሁዋላ ፣ በአቶ ሀይለማርያም የስልጣን ጊዜ የመጣ ክስተት መሆኑንና አለመሆኑን አላብራሩም።

አንድነት ፓርቲ በአዳማ/ናዝሬት የተሰካ የተቃውሞ ሰልፍ አደረገ

ጳግሜ ፬(አራት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ፓርቲው በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች በተገኙበት ገዢው ፓርቲ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ከማውገዝ በተጨማሪ ህዝቡ ለእውነተኛ ለውጥ እንዲነሳ ጥሪ አድርጓል።

ሰልፈኛው ሲያሰማቸው ከነበሩት መፈክሮች መካከል ጥያቄያችን ህገመንግስታዊ ነው፣ ውሸት ሰልችቶናል፣ ስራ መግኘት መብታችን ነው፣ ጸረ ሽብር ህጉ በራሱ አሸባሪ ነው፣ መንግስት፣ የኑሮ ድጎማ ያድርግልን፣  ድህነት በወሬ አይጠፋም፣ ርእዮት አለሙ አሸባሪ አይደለችም፣ የታሰሩ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና ጋዜጠኞች ይፈቱ የሚሉና ሌሎችም መፈክሮች ተሰምተዋል።

በተለያዩ የስራ ዘርፎች የተሰማሩ የከተማው ነዋሪዎች እና የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በተሳተፉበት በዚህ ሰልፍ ላይ በቅርቡ ራሳቸውን ከአንድነት የህዝብ ግንኙነት አመራር ቦታ ያገለሉት ዶ/ር ሀይሉ አርአያን ጨምሮ ሌሎችም ንግግሮችን አድርገዋል።

የአንድነትን ሰልፍ ለማደናቀፍ የከተማዋ ባለስልጣናት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የተለያዩ ሙከራዎችን ቢያደርጉም፣ ፓርቲው ዝግጀቱን በጥሩ ሁኔታ አጠናቋል።

አንድነት ፓርቲ የጀመረው የሶስት ወር ዘመቻ መስከረም 5 በአዲስ አበባ በሚያደርገው የተቃውሞ ሰልፍ ይጠናቀቃል።

 

አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ በቢሮክራሲው መማረሩን ገለጸ

ጳግሜ ፬(አራት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ታዋቂው አትሌት ሻለቃ ሀይሌ ገብረስላሴ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ቢሮክራሲ የኢንቨስትምንት ስራ  ለመስራት ዋነኛው እንቅፋት መሆኑን ከሪፖርተር ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ገልጿል። የመብራትና ውሀና መንገድ ችግሮችን በጋራ መቋቋም ይቻላል ያለው ሀይሌ ፣ ቢሮክራሲው ከፍተኛ ችግር መሆኑን ገለጿል።

ሀይሌ እንደሚለው የቢሮክራሲው ዋና ምክንያት በራሳቸው የሚወስኑ ባለስልጣናት መጥፋታቸው ነው። በተለያዩ ሀላፊነት ላይ ያሉ ባለስልጣናት በራሳቸው እንዲወስኑ እስካልተደረገ ድረስ ችግሩ ሊፈታ እንደማይችልም ተናግሯል።

በኬንያ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጡ የተለያዩ ድርጅቶች በመኖራቸው ህዝቡ አማርጦ እንደሚገዛ የገለጸው ሀይሌ፣ በኢትዮጵያ እንዲህ አይነት እድል ባለመኖሩ መስሪያ ቤቱ ውጤታማ አለመሆኑን አብራርቷል። መብራት ሀይልም እንዲሁ በተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ውስጥ ሊገባ እንደሚገባው አትሌቱ መክሯል።

አትሌት ሀይሌ በቅርቡ ወርቅ በማውጣት ስራ ላይ ለመሰማራት ማቀዱንም ገልጿል። የኢትዮጵያ አትሌቶች በከፍተኛ የኢንቨስትመንት ስራ ላይ መሰማራታቸውን አክሎ ተናግሯል።

ታዋቂው አትሌት ፕሬዚዳንት የመሆን ፍላጎት እንዳለው መግለጹ ይታወሳል።

 

ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ በኢትዮጵያ ውስጥ አክራሪነት የለም የሚሉ የተቃዋሚ ድርጅቶች አጥፊዎች፣ከሃዲዎች ናቸው አሉ

ጳግሜ ፬(አራት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ጠ/ሚኒስትሩ ትላንትና እና ዛሬ ለሕትመት በበቃው ከመንግስታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ላይ እንደተናገሩት “የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በርግጥም ለኢትዮጽያ ሕዝብ ዴሞክራሲ፣መልካም አስተዳደር ልማትና ሠላምን ለማምጣት አጀንዳ አድርገው የሚንቀሳቀሱ ከሆነ አክራሪነትንና ሽብርተኝነትን ከመንግስት ጎን ተሰልፈው ሊያወግዙ ይገባል ብለዋል፡፡

” በኢትዮጽያ አክራሪነትና ሽብርተኝነት የለም ብለው የሚያስቡ ከሆነ እነዚህ ሰዎች በኢትዮጵያ ውስጥ የሉም ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን በዓለም ላይ እየተካሄደ ያለውን አያውቁም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ስራና ሕዝቡን ለመምራት የሚያስችል ትልቅ ኃላፊነትና ብቃቱ የላቸውም ማለት ነው፡፡  ብቃቱ አለን ብለው የሚያስቡ ከሆነ ዓለማዊውንና አገራዊ ሁኔታ በአግባቡ ገምግመው ሸብርተኛነትን እንደዚሁም አክራሪነትንና ጽንፈኝነትን በኢትዮጽያ እያቆጠቆጠ የመጣና ሕዝቡን በግላጭ እየጎዳ ያለ እንደሆነ ማንም
የሚያውቀውን እየካዱ የሚሄዱ ከሆነ እነዚህ ሰዎች ዓላማቸው ሰላማዊ፣ሕጋዊና ለአገሪቱ የሚጠቅም የፖለቲካ ስርዓት
ውስጥ ተወዳድረው ለማሸነፍ የተዘጋጁ ኃይሎች አይደሉም ማለት ነው” ብለዋል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሁንም ቢሆን ከድርጊታቸው ታቅበው በሰላማዊ፣ሕጋዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ተወዳድረው ማሸነፍ እንዳለባቸው የመከሩት አቶ ኃ/ማርያም ፣ ተወዳድረው ማሸነፍ ሲያቅታቸው ከእኔ የቀረ እንደሆነ አገሩቱዋ ትቀጣጠል

ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የሚገቡ ከሆነ አጥፊዎች ናቸው ማለት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አቶ ኃ/ማርያም ባለፈው ሳምንት እሁድ በተካሄደውና በመንግስት በሚደገፈው የአደባባይ ሰልፍ ከ600ሺ በላይ ሕዝብ

መውጣቱን አስታውሰው ይህ አክራሪ ኃይሎች ከሕዝቡ መነጠላቸውን ያሳያል ብለዋል፡፡ አክራሪና ጽንፈኛ ኃይሎች ከሕዝቡ ከተነጠሉ አስተዳደራዊና ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ቀላል ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት እሁድ በአዲስአበባ በመስቀል አደባባይ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠርተውታል የተባለው ሰልፍ በቀጥታ በመንግስት የተመራ ሲሆን የቀበሌ ሹማምንት በየቤቱ እየሄዱ ነዋሪዎች በሰልፉ ላይ እንዲገኙ የግዳጅ ፊርማ ሲያስፈርሙ እንደነበር መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡

የአላሳድ መንግስት የኬሚካል መሳሪያ አለመጠቀሙን አስታወቀ

ጳግሜ ፬(አራት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ፕሬዚዳንቱ በህዝቤ ላይ የኬሚካል የጦር መሳሪያ የምጠቀምበት ምንም ምክንያት ለም በማለት ለአንድ የአሜሪካ የቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል።

አሜሪካ ሶሪያን ብትደበድብ አንዳንድ ደጋፊ አገሮች አጸፋዊ መልስ ለመስጠት መዘጋጀታቸውንም አላሳድ አክለው ገልጸዋል። ይሁን እንጅ እነዚህን አገሮች  በስም ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

አለም በሶሪያ ላይ ስለሚወደው የሀይል እርምጃ ተከፋፍሎአል። ፕሬዚዳንት ኦባማ በሶሪያ ላይ እርምጃ ካልተወሰደ ሌሎች አምባገነን መንግስታት ህዝባቸውን በተመሳሳይ መንገድ ከመግደል አይመለሱም በማለት ይከራከራሉ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ፣ ጉዳዩን የሚያጣራው የድርጅቱ ልኡክ ሪፖርቱን እሰከሚያቀርብ ድረስ አሜሪካ እርምጃ ከመውሰድ እንድትቆጠብ ጠይቀዋል። ፈረንሳይን ጨምሮ ሌሎች የአውሮፓ አገራትም ይህን 

Advertisements
Aside | This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s